Monday, March 10, 2014

የ40/60 ቤቶች ዲዛይን ተለወጠ



መንግሥት የዜጐችን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ ከጀመራቸው ፕሮግራሞች አንዱ የሆነው የ40/60 ቤቶች ፕሮግራም የቤት ዲዛይን ተለወጠ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ40/60 ቤቶች ፕሮግራም ምዝገባ ካካሄደ በኋላ የቤቶች ዲዛይን እንዲከለስ ተወስኖ ነበር፡፡ ለ40/60 ቤቶች የተሠሩት አዳዲሶቹ ዲዛይኖች ከፍታቸው ከ18 እስከ 24 ፎቅ ይደርሳል፡፡ የቀድሞው ዲዛይን ባለ 12 ፎቅ ሲሆን ግንባታቸው በተጀመሩ ቦታዎች ይኼው ዲዛይን ይቀጥላል ተብሏል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ባወጣው መግለጫ፣ አዳዲሶቹ ዲዛይኖች በየደረጃው ለአስተያየት ይቀርባሉ፡፡ ይህ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እንደተጠናቀቀ አዳዲሶቹ ዲዛይኖች ተግባራዊ እንደሚደረጉ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለ40/60 ቤቶች ፕሮግራም ባካሄደው ምዝገባ 164 ሺሕ ነዋሪዎች ተመዝግበዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ሰባት ሺሕ ተመዝጋቢዎች ባለአንድ መኝታ፣ 72 ሺሕ ተመዝጋቢዎች ባለሁለት መኝታ፣ 85 ሺሕ ተመዝጋቢዎች ባለሦስት መኝታ መኖሪያ ቤት ለማግኘት ተመዝግበዋል፡፡


ነገር ግን ቀደም ብሎ መንግሥት ለባለአንድ ክፍል ብዙ ተመዝጋቢዎች ይኖራሉ ብሎ በማሰቡ የተሠራው የ40/60 ቤቶች ዲዛይን ባለአንድ መኝታ ቤቶች ላይ ትኩረት አድርጐ ነበር፡፡

ዲዛይኑ በወቅቱ እንዲከለስ የተደረገው የተመዝጋቢዎችን ፍላጐት ታሳቢ ባደረገ መንገድ እንዲሆን በመፈለጉ ነበር፡፡ ነገር ግን አርክቴክቶቹ አዲስ ሐሳብ ይዘው በመምጣታቸው የቤቶች ከፍታ በእጥፍ እንዲጨምር ተደርጓል፡፡

አዳዲሱ ዲዛይን ለንግድና ለማኅበራዊ አገልግሎት መስጫነት የሚያገለግሉ ክፍሎች አረንጓዴ ቦታዎችና መዝናኛ ማዕከላት ይኖሩታል ተብሏል፡፡

ይህ ዲዛይን ተግባራዊ ከተደረገ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ታሪክ የመጀመርያው ይሆናል የሚል እምነት አለ፡፡ በአነስተኛ ሥፍራ ላይ በርካታ ሰዎችን የሚይዝ ዲዛይን በመሆኑ ጠቀሜታው የጐላ ነው የሚሉ ባለሙያዎችም አሉ፡፡  
http://ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment