አቶ ተካ አስፋው ጀባ የተባሉ የቅመማ ቅመም ነጋዴ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ መርካቶ በሚገኘው ምዕራብ ሆቴል ከሊፍት ስር ባለ ጉድጓድ ውስጥ ሞተው ተገኙ፡፡ የ65 አመት እድሜ ባለፀጋ የሆኑት አቶ ተካ እሁድ ታህሳስ 21 ቀን 2005 ዓ.ም ከጠዋቱ አራት ሰዓት አካባቢ ጀምሮ ከሚሠሩበት የቅመማ ቅመም ንግድ መደብራቸው እንደጠፉ የሚናገሩት ቤተሰቦቻቸውና የስራ ባልደረቦቻቸው፤ ከአራት ቀናት በኋላ ታህሳስ 24 ቀን 2005 ዓ.ም ምዕራብ ሆቴል ውስጥ ከሊፍት ስር ወድቀው መገኘታቸውን ከፖሊስ ተደውሎ እንደተነገራቸው ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
ሟች በጠፉ ማግስት በኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች የአፋልጉኝ ማስታወቂያ ማስነገራቸውን እንዲሁም በአካባቢው ለሚገኘው 4ኛ ፖሊስ ጣቢያ ስለመጥፋታቸው ማስታወቃቸውን የገለፁልን ቤተሰቦቻቸው፤ እያሽከረከሯት የነበረችው መኪና ድሬ ታወር አካባቢ ቆማ መገኘቷንም ተናግረዋል፡፡
የወላጅ አባታቸውን መጥፋትና በኋላም ሞቶ መገኘት በሚኖሩበት አሜሪካን ሃገር ሆነው በስልክ መስማታቸውን የነገሩን አቶ ፈለቀ ተካ፤ ዝርዝር ጉዳዩን እዚህ ከመጡ በኋላ ከሟች የስራ ባልደረቦችና እዚህ ካሉ ቤተሰቦቻቸው መረዳታቸውን ለዝግጅት ክፍላችን ገልፀዋል፡፡
ሟች የሆቴል አገልግሎትን ጨምሮ በተለያዩ የንግድ ስራዎች በመርካቶ አካባቢ ይሠሩ እንደነበርና እስከ እለተሞታቸውም በቅመማ ቅመም ንግድ ይተዳደሩ እንደነበር አቶ ፈለቀ ገልፀውልናል፡፡ የስምንት ልጆች አባት የነበሩት አቶ ተካ ከሁለቱ ልጆቻቸው በስተቀር ሁሉም በአሜሪካን አገር እንደሚኖሩ ከቤተሰቦቻቸው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ከሟች ልጆች አንዱ የሆኑት አቶ ግዛው ተካ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉት መሆኑን በመግለፅ የሟች አስከሬን ከአንድ ሜትር ተኩል በማይበልጥ ጉድጓድ ውስጥ ሲገኝ አብሮ የእጅ ሠአት፣ ሞባይል ስልካቸው፣ የተለያዩ ቼኮችና 2700 ብር ጥሬ ገንዘብ መገኘቱን ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል፡፡ በወቅቱ ሟች ያሽከረክሯት የነበረችው መኪና ቁልፍና የቁም ሣጥን ቁልፍ ግን እስካሁን አለመገኘቱ ግራ እንዳጋባቸውና ይህም እንዳሣሠባቸው ገልፀዋል፡፡ እሁድ ጠዋት ላይ ጭላሎ ሆቴል አካባቢ ቀጠሮ አለኝ ብለው ከቤት መውጣታቸውን የሚናገሩት የሟች ቤተሠቦች እስካሁን ከማን ጋር ተቀጣጥረው እንደነበር አለመታወቁ እንዳሣሠባቸው ይህንንም ፖሊስ እንዲያጣራ ማሣወቃቸውን ገልፀውልናል፡፡ ከቤት የወጡ እለትም ስልካቸው እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ድረስ ላይ በተደጋጋሚ ሲደወል ነገር ግን እንደማይነሳ አስረድተዋል፡፡
የምዕራብ ሆቴል የካፍቴሪያ ሃላፊ አቶ አዳነ ሸለሙ ስለሁኔታው ብዙም እንደማያውቁና ግለሰቡ እንደማንኛውም ተስተናጋጅ ለመስተንግዶ ወደ ሆቴሉ ከምጣታቸው በስተቀር የብዙ ቀን ቆይታ በሆቴሉ እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ ከተፈጠረው አደጋ ጋር በተያያዘም የሆቴሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ተፈራ ክፍሌን ጨምሮ በወቅቱ የነበሩ ጥበቃዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን አቶ አዳነ ተናግረዋል፡፡
ጉዳዩን እየተከታተለ ከሚገኘው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ “ፍቃድ ያስፈልጋል” በመባላችን ሳይሳካልን ቀርቷል፡፡
http://www.addisadmassnews.com
No comments:
Post a Comment