በዮሐንስ አንበርብር
በትግራይ ክልል ከ1‚300 በላይ የሚሆኑ የሕግ እስረኞችን ያስጠለለው የአዲግራት ወህኒ ቤት ባለፈው ረቡዕ ከረፋዱ አምስት ሰዓት ተኩል አካባቢ ተደርምሶ 14 እስረኞች ሲሞቱ፣ ከ35 በላይ ደግሞ በከባድ ሁኔታ መጎዳታቸውን ምንጮች ገለጹ፡፡ እስር ቤቱ በምን ምክንያት እንደተደረመሰ ለማወቅ እንዳልቻሉ በወቅቱ በአካባቢው የነበሩ የዓይን እማኞች ለሪፖርተር የገለጹ ሲሆን፣ እስረኞቹን ለማትረፍ ሦስት ሎደሮችና በርካታ ወታደሮች ሲረባረቡ ማየታቸውን ገልጸዋል፡፡
በተደረገው ርብርብም 35 የሚሆኑ እስረኞችን በሕይወት ማትረፍ
ቢቻልም፣ በከባድ ሁኔታ የተጐዱ መሆናቸውን፣ 14 እስረኞች ግን በፍርስራሹ ሥር ሙሉ ለሙሉ በመቀበራቸው በተደረገው ርብርብ ሕይወታቸውን ማትረፍ ሳይቻል ወዲያውኑ መሞታቸውን አስረድተዋል፡፡
አደጋው የደረሰው ከረፋዱ አምስት ሰዓት ተኩል አካባቢ በመሆኑ ሎደሮቹን በፍጥነት ለማግኘት እንደተቻለ፣ በዚህም ምክንያት የአብዛኞቹን ሕይወት ሊተርፍ ችሏል የሚሉት እነዚሁ የዓይን እማኞች፣ አደጋው በምሽት ተከስቶ ቢሆን ኖሮ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር ይችል እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው 35 እስረኞች አዲግራት ሆስፒታል ተኝተው እየታከሙ መሆኑ ታውቋል፡፡
የደረሰውን አደጋ በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የትግራይ ክልል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ኃላፊን አቶ ፈረደ የሺወንድምን ያነጋገርን ቢሆንም፣ አደጋው ስለመከሰቱ ብቻ አረጋግጠው ተጨማሪ መረጃ ከአዲግራት ወህኒ ቤት ማግኘት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ የእስር ቤቱ ኃላፊ የሆኑት ኮማንደር ይትባረክ አለነን በግል ስልካቸውም ሆነ በቢሯቸው ለማግኘት የተደረገው ጥረት የሉምና ስብሰባ ላይ ናቸው በሚል ምክንያት አልተሳካም፡፡
http://www.ethiopianreporter.com
No comments:
Post a Comment