Wednesday, October 30, 2013

የሰሜን ዕዝና የአየር ኃይል ዋና አዛዦች በሌሎች ተተኩ



-የፓርላማው አባል የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕግ አማካሪ ሆኑ

በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አቅራቢነትና በፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ አማካይነት የጄኔራል መኮንኖች ሹመት ከተካሄደ በኋላ፣ በመከላከያ ሠራዊቱ አመራሮች ላይ የኃላፊነት ሽግሽግ ተካሄደ፡፡

በሽግሽጉ መሠረት ኤርትራ ኢትዮጵያን ከወረረች ጀምሮ የሰሜን ዕዝ ዋና አዛዥ በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩት ታዋቂው ሌተና ጄኔራል ሰአረ መኮንን በተሻለ ኃላፊነት ወደ ማዕከል እንዲመለሱ መደረጉን ምንጮች ገልጸዋል፡፡



በሰሜን የአገሪቱ ክፍል በተለይም የኤርትራን ወታደራዊ እንቅስቃሴ የመከታተልና የመመከት ኃላፊነት በተሰጠው የመከላከያ ሠራዊቱ የሰሜን ዕዝ አወቃቀር ላይ ማሻሻያ መደረጉን ምንጮች ያመለክታሉ፡፡ በተደረገው ማሻሻያ መሠረት የሰሜን ዕዝ ዋና አዛዥ የነበሩት ሌተና ጄኔራል ሰአረ ወደ ማዕከል እንዲመለሱ ሲደረግ፣ በምትካቸው ሜጀር ጄኔራል ዮሐንስ ወልደ ጊዮርጊስ ተሹመዋል፡፡ ሶማሊያ የዘመተውን ሠራዊት የመሩና በተለያዩ ኃላፊነቶች የሠሩ መሆኑ ታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የአየር ኃይል ዋና አዛዥ በነበሩት ሜጀር ጄኔራል ሞላ ኃይለ ማርያም ምትክ ሜጀር ጄኔራል አደም መሐመድ መተካታቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ሜጀር ጄኔራል አደም በአየር ኃይል አብራሪነት ያገለገሉ ሲሆን፣ በመከላከያ ሠራዊት የዘመቻ መምሪያ ኃላፊ፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ደግሞ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በሚወዛገቡባት የአቢዬ ግዛት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ምክትል አዛዥ የነበሩ መሆናቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የአገር መከላከያ ሚኒስቴር በሌሎች ጄኔራል መኮንኖች ኃላፊነቶች ላይም ሽግሽግ ማድረጉን የገለጹት ምንጮች፣ ከአየር ኃይል አዛዥነታቸው የተነሱት ሜጀር ጄኔራል ሞላ እንደ ሌተና ጄኔራል ሰአረ ወደ ማዕከል ለከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት መሾማቸውን ምንጮች አስረድተዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት የተደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ላለፉት አሥር ዓመታት በላይና በአሁኑ ወቅትም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል በመሆን እያገለገሉ የሚገኙት አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ፣ የጠቅላይ ማኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሕግና ፍትሕ አስተዳደር አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ በመሆን ተሹመዋል፡፡

አቶ አስመላሽ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግንባር ቀደም የሥራ ኃላፊነት በሆነው የሕግ ማውጣት ተግባር በስተጀርባ ቁልፍ ከሚባሉት ግለሰቦች መካከል በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ባገኙት የሕዝብ ውክልና ባሳለፏቸው በርካታ ዓመታት የምክር ቤቱ የሕግና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡

የሚመሩት ቋሚ  ኮሚቴ ለፓርላማው የሚቀርቡ ረቂቅ ሕጐችን በተለይም ሕግና አስተዳደርን የተመለከቱትን በዋናነት የሚመለከት ሲሆን፣ የአገሪቱ የሕግና የፍትሕ ሥርዓት የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማትንም የመከታተልና የመቆጣጠር ኃላፊነት አለው፡፡

በቅርቡ በአቅም ማነስ ምክንያት ከኃላፊነት የተነሱት የፍትሕ ሚኒስትሩ አቶ ብርሃን ኃይሉ ከመሰናበታቸው አንድ ቀን በፊት ለፓርላማው ያቀረቡትን ሪፖርት በመተቸትና የሚኒስቴሩን ጉድለቶች በማስረዳት እንዲያስተካክሉ አቶ አስመላሽ መመርያ መስጠታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment