Wednesday, July 4, 2012

የዓለም ደቻሳ አስከሬን አዲስ አበባ ገባ


-    የቀብር ሥርዓቷ ዛሬ በትውልድ ሥፍራዋ ይፈጸማል

በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽሕፈት ደጃፍ አጠገብ በአሠሪዋ መሬት ለመሬት ስትጐተትና ስትደበደብ በማኅበራዊ ድረ ገጾች የታየችው፣ በኋላም አወዛጋቢ በሆነ ሁኔታ ራሷን አጠፋች የተባለችው የ33 ዓመቷ ኢትዮጵያዊት ዓለም ደቻሳ አስከሬን ትናንትና አዲስ አበባ ገባ፡፡

ሕይወቷ ካለፈ አራት ወራት ሊሞላ ቀናት ብቻ የቀሩት የዓለም ደቻሳን አስከሬን፣ ትናንትና ሰኔ 26 ቀን 2004 ዓ.ም. አባቷና ወንድሞቿ ከቦሌ ጉምሩክ የተረከቡ ሲሆን እንደተፋቱ የሚነገርለት የልጆቿ አባት ደግሞ ከአጥር ውጭ ሆኖ ሲጠብቅ ታይቷል፡፡

የሟች ዓለም ደቻሳ ታናሽ ወንድም አቶ ለታ ደቻሳ አስከሬኑን በተረከቡበት ወቅት “የኛን ሐዘን ያየ ወደ ዓረብ አገር ሄዶ ለመሥራት አይነሳሳም፡፡ ዓለም ለእናትና ለአባቷ ረዳት ነበረች፡፡ እዚሁ ያለንን ተካፍለን ብንኖር ይሻል ነበር፤” በማለት እንባ እየተናነቃቸው ተናግረዋል፡፡




አባቷና ወንድሞቿ በተገኙበት ከቦሌ አስከሬኗ ጉምሩክ ወጥቶ ከአዲስ አበባ  180 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ምዕራብ ሸዋ አቡና ግንደበረት ተጓጉዟል፡፡
አቶ ለታ እንዳሉት፣ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ዛሬ ከቀኑ በስድስት ሰዓት ላይ ሟች በምትከተለው የፕሮቴስታንት እምነት መሠረት በግንደበረት ይፈጸማል፡፡

የዓለም አስከሬን ከጉምሩክ ሲወጣ ሌላ አንድ አስከሬን አብሮት ነበር፡፡ የአስከሬኑን ተቀባዮች ለማነጋገር ቢሞከርም፣ ተረካቢዎቹ “ከዓረብ አገር በሰው ተልኮልን ነው፤” ከማለት ውጭ ተጨማሪ መረጃ ሊሰጡ አልፈቀዱም፡፡

“በሊባኖስ በሞተችው ኢትዮጵያዊት አሠሪ ላይ ክስ ተመሠረተ” በሚል ርዕስ እሑድ መጋቢት 9 ቀን 2004 ዓ.ም.፣ በሊባኖስ የኢትዮጵያ ቆንስላ ኃላፊ የሆኑትን አቶ አሳምነው ደበሌ ቦንሳን ጠቅሰን እንደዘገብነው፣ በሊባኖስ በኢትዮጵያውያን የቤት ሠራተኞች ላይ የሚታየው ችግር አስከፊ ገጽታ አለው፡፡ እረፍት አይሰጣቸውም፤ ምግብ ይከለከላሉ፤ ሌላው ቀርቶ የሠሩበት ደመወዝ እንኳን በአግባቡ አይሰጣቸውም ከዚህም በላይ ዱላና ግድያ ይፈጸምባቸዋል፡፡

አሁንም ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች በሕገወጥ መንገድ ወደ ሊባኖስ መግባታቸው አልቀረም፡፡ በቤይሩት ሕጋዊ የቤት ሠራተኛ የለም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም የዜጐችን መብት የሚያስጠብቅ የጋራ የሥራ ስምምነት ላይ ካልተደረሰ ኢትዮጵያውያን ወደ ቤይሩት እንዳይሄዱ እገዳ ከጣለ ከሦስት ዓመት በላይ አስቆጥሯል፡፡

በሕገወጥ መንገድ ሊባኖስ የገባችውና ለሦስት ወራት ያህል በቤት ሠራተኝነት ያገለገለችው ዓለም ደቻሳ፤ ከአስከሬኗ ጋር የተላከው መረጃ  የአሟሟቷ ሁኔታ ራሷን በማነቅ እንደሆነ ያሳያል፡፡ በወቅቱ ስለአሟሟቷ ሁኔታ ተጠይቀው የነበሩት አቶ አሳምነው በዓለም ድንገተኛ ሞት ጥርጣሬ እንዳላቸው መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡ የሊባኖስ መንግሥት በተደጋጋሚ በሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች አሟሟቷን እንዲያጣራና ውጤቱን እንዲገልጽ ቢጎተጎትም፣ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሏል፡፡

ሟች ዓለም ደቻሳ የሁለት ልጆች እናት ነበረች፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/

No comments:

Post a Comment