- ጉዳዩን ፌዴራል ፖሊስ ይዞታል
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በካዛንቺስ ሱፐር ማርኬትና በኢትዮጵያ ልማት ባንክ መካከል ከሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንድነት ቅርንጫፍ መጠኑ ያልታወቀ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ፣ ሰኔ 17 ቀን 2004 ዓ.ም. ሌሊት መዘረፉን ምንጮች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡
የባንኩ ቅርንጫፍ የጥበቃ ሠራተኞች ያሉት ቢሆንም፣ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ የቅርንጫፉ በሮች በቁልፍ ተከፍተው መጠኑ ያልታወቀው ገንዘብ መወሰዱን የገለጹት ምንጮች፣ ድርጊቱ ለረጅም ጊዜ ጥናት ተደርጐበት የተፈጸመ ሳይሆን እንደማይቀር ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡
በባንኩ ላይ ተፈጸመ ስለተባለው የዘረፋ ወንጀል ማብራሪያ እንዲሰጡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ኃላፊ አቶ ይስሀቅ መንገሻ፣ ‹‹ድርጊቱ በፖሊስና በሕግ ሰዎች ስለተያዘ ከዚህ በላይ መናገር አልችልም፤›› ብለዋል፡፡
ባንኩ ምንም እንኳን በአሁኑ ጊዜ መደበኛ ሥራውን እየሠራ ቢሆንም፣ የጥበቃ ሠራተኞች ባሉበት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ መዘረፉ ለደንበኞችና ለሠራተኞች እንቆቅልሽ ሆኖባቸዋል፡፡
ተዘርፏል ስለተባለው የገንዘብ መጠን እንዲገልጹ የተጠየቁት አቶ ይስሀቅ፣ የተፈጸመው ዝርፊያ በሕግ የተያዘ መሆኑን ከመናገር ውጪ፣ ተጨማሪ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የቅርንጫፉ ሠራተኛ ግን ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ ተዘርፏል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል የተዘረፈው ገንዘብ ከዚህ እንደሚበልጥ የሚናገሩ አሉ፡፡
በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ ከሪፖርተር ለቀረበለት ጥያቄ በሰጠው ምላሽ፣ ጉዳዩ በፌዴራል ፖሊስ መያዙንና በምርመራ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡ የፌዴራል ፖሊስን ማብራሪያ ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡
No comments:
Post a Comment